You can reach our office at anytime at eotcdcp.assn@gmail.com
የካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓም
በሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት የቀድሞ በዓታ ማርያም ገዳም አበመኔት የነበሩት ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል በየካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓም በሰው እጅ በግፍ ተገለዋል ፤ የአባታችን የመታሰቢያ መርኃ ግብር በትውልድ መንደራቸው ወላይታ ዴልቦ መድኃኔዓለም ቤተክርስትያን ከትደረገ በኃላ የቀብር ሥነ ስርዓታቸውም በዚሁ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።
ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል ይባላሉ ትውልዳቸው በወላይታ ሀገረስብከት ዴልቦ ከተማ ሲሆን የዕድሜያቸውን ብዙ ዘመን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተማሪነት እና በአገልግሎት ቆይተዋል።
በጎንደር አከባቢ ጉባኤ ዘርግተው የሚያስተምሩ እና ጩገ ማርያም ገዳም አበምኔት ሆነው እያገለገሉ ሳለ ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸው በድንገት የካቲት ፲፮ ቀን ከዚህ ዓለም የሥጋ ድካም ወደማያልፈው ዓለም አልፈዋል።
አባታችን ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል ከበዓታ ማርያም እስከ ዋልድባ በልዩ ልዩ አገልግሎት ያገለገሉ ሲሆን የአባታችንን ግድያ በተመለከተ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ምርመራውን አድርጎ ገዳዮቻቸው ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ዝርዝር መረጃውን የጎንደር ሀገረ ስብከት ተከታትሎ ለማህበረ ምዕመናንን ሊያቀርብ ይገባል።
የክቡር አባታችን የከበረች በረከታቸው ይደርብን በሁላችንም ይደረብን አሜን።
መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በአዲስ አበባ ፉሪ አካባቢ ቀሲስ ዓባይ መለሰ የተባሉ ካህን ቅዳሴ ጨርሰው ወደ ቤታቸው በመሄድ ላይ እያሉ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል። ይህንን አስነዋሪ ድርጊት ለማጋለጥ በሰዓቱ የነበረውን ኹኔታ በምስልና ቪዲዮ ለማስረጃ ለመያዝ የሞከሩ ሰዎች ቢኖሩም በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ሞባይል በመሰብሰብ የቀረጹትን ምስልና የቪዲዮ ማስረጃ እንዳጠፉባቸው ታማኝ ምንጮች ዘግበውታል። ጉዳዩ ቀደም ብሎ ከፍ ባለ ዛቻና ማስፈራሪያ የታጀበ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን በዚህ ኹኔታ ግን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ያደርጉታል የሚል እምነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡
የመከራው ዶፍ ከየት ወደየት እየሄደ ይሆን?
ይገርማል! ጂጅጋ ካህናት በእሳት ተቃጥለዋል። በወለጋ ሰንበት ተማሪው በአደባባይ ተረሽኗል። በሖሮ ጉድሩ ካህናት ታርደዋል። በሻሸመኔ ምእመናን በስናይፐር ተጨፍጭፈዋል። አርሲ ካህናት ተመርጠው ታርደዋል። አምስት ዓመት ሙሉ ንጹሓን ያለ ከልካይ ሲጨፈጨፉ ኖረዋል። ገርበ ጉራቻ ላይ መስቀል የጨበጠ ሻሽ የጠመጠመ ካህን በጥፊ ተመቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ ወጣቶች በታጣቂዎች በመንግሥት ታጣቂዎች እየተገደሉ ነው። ታቦት ላይ አስለቃሽ ጭስ ተተኩሷል። እሥርና ግርፋቱን ቤት ይቁጠረው። ዛቻና ማስፈራሪያውን አምላክ ይመልከተው። አሁን ደግሞ ቀዳሽ ካህን በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል። ነገ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሌላ መርዶ እንሰማለን። መሬት የወረደ እና ራስን መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ እስካልጀመርን ድረስ 5 ኪሎ ላይ መርዶ መስማታችን የማይቀር ነው።
በሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃያማኖት አንብሮተ ዕድ ከተሾሙት ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት በቀድሞ ስማቸው አባ ኃይለማርያም መለሰ ዶ/ር በጵጵስና ስማቸው ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጪ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊና የድሬ ደዋና የጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። ብፁዕነታቸው ለረጅም ጊዜ ከሀገር ውጪና በሃገር ውስጥ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ባለመቻሉ ዛሬ መጋቢት ፲፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን አሜን።